28.10.14

የታለች ያቺ ወፍ?


"የታለች ያቺ ወፍ" የተባለውን ግጥም... ደራሲ አናኒያ መኮንን  ananyamekonnen.blogspot.com በሚባለው ድህረ ገጽ ካስቀመጠው ወራቶች አልፈዋል። እኔም እንደማንኛውም አንባቢ አንብቤ በአድናቆት የተሞሉትን ቃሎቼን ብወረውርም፥ የግጥሙ ቅኔ ልቤን ሰለነካው ለግጥሙ የሚሆን ስእሌን መሞነጭጨር ጀመርኩ። ወራቶችም አለፉ... በማስታወሻ ወረቀት የተሞነጫጨረው ስእል ቀን ወጣለትና ተሰሎ አለቀ። ደራሲ አናኒያ ሰለሰጠኝ ውበት ደግሜ እያመስገንኩ የደራሲውን ግጥምና የእኔን ስእል እነሆ።


የታለች ያቺ ወፍ
ደራሲ አናኒያ መኮንን

ያኔ ልጅ እያለሁ - ሰላም የምትለኝ
በሚያስደምም ዜማ - ልቤን የምትቃኘኝ
ቀኑ ደስ እንዲለኝ - ተስፋ የምትሰጠኝ
የታለች ያቺ ወፍ? - ዛሬ ስትናፍቀኝ
ከእንቅልፌ ስነቃ - ደስ በሚለው ዜማ
ኮለል ብሎ መጥቶ - በጆሮዬ ሲሰማ
የቀኑን ብሩህነት - ለነብሴ አብስራ
ታነቃቃኝ ነበር - መንፋሴን አድሳ
የታለች ያቺ ወፍ? - ዛሬ ስፋልጋት
ምነው አልዘፈነች - ነብሴ ሲናፍቃት
ምናል ብትመጣ - ልትሰጠኝ እርካታ
ዜማውን አፍልቃ - ብትሆነኝ እርጋታ
ግና ብትመጣስ - እንግባባ ይሆን
እንዲህ ተለያይተን - ብዙ አመቶች ከርመን
አንድ ያመሳሰለን - ጓደኞች ያረገን
የዋህነት ነበር - በፍቅር ያቀረበን
አሁን ታደገና - የዋህነት ቀርቷል
እንደ እባብ በተንኮል - መተያየት በዝቷል
መተዛዘን ቀርቶ - መጠቃቀም ሆኗል
ሀሳብ ልብም - ሲባክን ይውላል
አሁን ወፏ መጥታ - ጓደኞቿን ጠርታ
ስትዘፍን ብትወል - ኦርኬስትራ ሰርታ
ማን ሊያዳምጣት ነው - በበዛ ጫጫታ
ማንስ ይሰማታል - ታስረን በሁካታ


After reading, Ananya Mekonnen poem

የሚገርም ግጥም…. እንደእኔ ተስምቷችሃል? ጆሮ ያለው ይስማ ያስኛል። 
የደራሲው ብእር ትለምልም። 

በረከት

22.10.14

ተለወጥ Change


ስሞኑን ያንንም ይህንንም ስሰራ ስነበትኩ። የስእል እቃዎቼ በየስፍራው ተበታትነዋል፥ አንዳንዴ ብዙ የሚስሩና የሚፈጠሩ ነገሮች ይበዙብኝና አንዱን ጀምሬ ሳልጨርስ ወደሌላው እዛወራለሁ። የፈጣሪ ስሙ ይክበርና ይመስገን አእምሮዬም ከመፍጠር  እጆቼ ከመስራት አላቋረጡም፥ ድሮ ድሮ ይህ የፈጠራ ስራ ደረቅረቅ ሲል ውስጤ ሁሉ ደስ አይለኝም ነበር። መቼም ስው...  የእግዚአብሔር ስው ሆኖ... ለበጎ የማይቀየር.... በበጎ የማያድግ ከሆነ ውስጡን በሚገባ መመርመር አለበትና። ታዲያ.... እኔም እያደርና እየዋለ የፈጠራ ሳራ መጣ አልመጣ.... ደረቀ አልደረቀ.... ብዬ ራሴን አላስጨናንቀውም። ስእሎቼን ከሳያልኩ በደስታና በጸሎት.... የሚሳልም ከሌለ በደስታና በጸሎት መቀበሉን ተማርኩ።
አንዳንዴ ሳናውቀው ተለውጠን እንገኛለን፥ መለወጣችን ሁሉ ለመልካምነት ከሆነ ብዙ ፍሬ እናፈራለን። ትግስቱን ትህትናውን አስተዋይነቱን....   እነዚህን ሁሉ እናፈራለን። ግን.... ግን መለወጣችን ለዓለም እና በዓለም ከሆነ  ፍሬ እንደማያፈራ ዛፍ ሆነናል። 
የአባታችንን የአብርሃምን ታሪክ ሳስበው በጣም ይገርመኛል። ከተወለደበት ከተከበረበት ሀገር ወጥቶ የት እንደሚሄድ ሳያውቅ በእግዚአብሔር ስለተጠራ ለመለወጥ አቤት ማለቱ ያስደንቀኛል። 
ለመለወጥ አቤት ማለት
ለመለወጥ ከጓዳ መውጣት
ለመለወጥ ዝግጁ መሆን 
እንዴት መባረክ ነው?
በተለይ በዚህ ዘመን መለወጣችን እንዴት ነው? መለወጣችን ለማን ነው? ስንለወጥስ ስንቶችንን አስደስተናል ወይስ አሳዝነናል? “Growth means change and change involves risk, stepping from the known to the unknown.” 

"By faith Abraham obeyed when he was called to go out to a place that he was to receive as an inheritance. And he went out, not knowing where he was going."  Hebrews 11:8

"አብርሃም የተባለው ርስት አድርጎ ሊቀበለው ወዳለው ስፍራ ለመውጣት በእምነት ታዘዘ፥ ወዴትም እንደሚሄድ ሳያውቅ ወጣ።"  ወደ ዕብራውያን 11:8

በረከት

18.10.14

አይረስ Iris

አምላካችን... በፍጥረቱ ውበት አይናችንን አጥግቧልና ቅዱስ ስሙ ይመስገን።  እኛም... የትም ሆነን የት... ሌሎችን በመልካምነታችን እናጥግባችው። ከአንደበታችን እንደ አበባ ያማረ ቃል ይውጣን።

በረከት

8.10.14

አንድ ቅጠል


ከእለታት አንድ ቀን አንድ ቅጠል ነበረ


 ግንዱና ከቅርንጫፉ ተለይቶ መኖር ጀመረ፥
 ዓለምም ብቻውን ወዝውዛ አጠወላለገችው። 
ውሎ ሲያድር.... ተጨመታተረና ተቀደደ።   


 በመቀደዱ ሲያዝንና ሲተክዝ... ዓለም መልኩ በማይመስለው ክር ስፋችው።


ተስፍቶ ሲኖር እያለ መጠውለጉ ባስብት። ልምላሜ ከሱ ፈጽሞ ራቀ። 


ዓለምም በውሸት ቀለሟ  አሳምራ ቀባችው።


 ቢገለብጡት... ለምለም የሚመስለው የዓለም ቀለም ባይኖረውም
 ለግዜው ተደስቶ መኖር ጀመረ።  


ሌሎች የውሽት ቀለማችውን እንደተቀቡ ጠወላልገው ሲፈረካከሱ አየ።


 በዚህ ግራ ተጋብቶ ሳለ... የተቀባው የውሽት ቀለም እየዋለና እያደረ መልቀቅ ጀመረ። ውስጡ ከመቼውም በላይ ደርቆና ተስነጣጥቆ ተስማው። ወዲያውኑ ወደግንዱና ወደቅርንጫፉ ለመመለስ ወስነና ተጓዘ።  


በመንገድ ላይ ሳለ በድንገትም ልምላሜነት ተስማው። 
ግንዱ ጋር ደርሶ ከቅርንጫፎቹና ከሌሎች ቅጠሎች ጋር አብሮአቸው በህብረት መኖር ጀመረ።
 ቅጠሉም ከመቼውም ይበልጥ ለምልሞና አብቦ ተገኘ።


ሉቃስ 15:11-32